በአዉደ ጳጉሜ 6 ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ለቀረበዉ ተቃዉሞ ማፍረሻ!

የጳጉሜ 6ን ሁለተኛ ተቃዉሞ ማፍረሻ!

በፋሲል ጣሰዉ ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል፡፡

 1. መግቢያ
  • መንደርደሪያ

ጳጉሜ 6፤ የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ የማን ነዉ? ስል የኢትዮጵያን ቀን መቁጠሪያ መጽሐፍ ከግሪጎሪያን አንፃር መፍጠር የቻልኩት ላለፉት 17 ዓመታት ያስተዋልኳቸዉን አምስት ተጨባጭ ተግዳሮቶች በማስቀረት የምሥራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃትና ፈጣን ምድረ ሰማይን መልሰን እንድንይዝ ብቻ ሳይሆን እነርሱም በምሥራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ጠባብ ቀዝቃዛና ቀርፋፋ ምድረ ሰማይ መወሰናቸዉን በማሳየት የኢትዮጵያን አፍሪካ ህዳሴ ከወዲሁ ለማቀላጠፍ ጭምር ነዉ፡፡

አምስቱ ተድጋሮቶች

 • በጳጉሜ ዉሥጥ የምጣኔ ሃብት አሰራር መሳሪያዎች ባለመፈጠራቸዉ የተነሳ ደመወዝ ለሰራተኛ፤ ቤት ሰርቶ ላከራየ የቤት ኪራይ ገቢ፤ ገንዘቡን ባንክ ለቆጠበ የቁጠባ ወለድ እና ለመንግስት የገቢ ግብር ጭምር አለመኖሩ፤

 

 • የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ወሮች በግሪጎሪያን ቀን መቁጠሪያ ወሮች በዉርስ በመተርጎማቸዉ የተነሳ ጳጉሜ በዘመናዊ መዛግብተ ቃላት ተዘሎ መገኘቱ፤

 

 • በምሥራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃት ምድር ዉስጥ የሚከሰቱት አራት መካከለኛ ተቃራኒ ወቅቶች እና አጭር የቀንና ለሊት ልዩነት የምናያቸዉና የምንኖረባቸዉ ቢሆኑም እስካሁን ድረስ በሳይነሳዊ ዘዴ ተመዝግበዉ ዘመናዊ ትምህርት ዉስጥ እንዲገቡ አለመደረጉ፤

 

 • የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ በምሥራቅ ምዕራ ሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃትና ፈጣን ምድር ዉሥጥ ሥራ ላይ መዋል ሲገባዉ ዝም መባሉ እና

 

 • የኢትዮጵያን ቀን መቁጠሪያ ይመለከታል በሚል በጥንተዊ አቡሻኽር አስተምህሮት ዘዴ እየተሰጠ የሚገኘዉ ትምህርት የምዕራብ ሰሜን ጠባብ ቀዝቃዛ ምድርን ጊዜ ንድፈ ሃሳብን መሆኑ ናቸዉ፡፡

የመጀመሪያዉን ተድጋሮት በ1991 ዓ.ም ላይ ያስተዋልኩት በጳጉሜ ዉስጥ ተሰርቶ የተገኘ ገቢ ከነሃሴ ወር ተሰረቶ ከተገኘ ገቢ ጋር ተደምሮ እንደ አንድ ወር ገቢ መታሰብ አለበት የሚል ድንጋጌ ከ1953 ዓ.ም. ገቢ ግብር ህግ ላይ ካነበብኩበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ተግባር መለወጥ አለብን የሚል ጭብጥ ይዤ በመነሳቴ ጭምር ነዉ፡፡ በመሆኑም በድንጋጌዉ መሰረት በጳጉሜ ዉስጥ በጀት ተበጅቶ ያልተተገበረዉ ለምንድን ነዉ? የሚለዉን ጥያቄ በወቅቱ የገንዘብና ኢኮኖሚ  ልማት ሚ/ር  በጀት መምሪያ ኃላፊ ለነበሩት ግለሰብ አቀረብኩ፡፡ ግለሰቡ በጳጉሜ ዉስጥ ለምን በጀት እንደማይሰራ  መልስ ባይሰጡኝም የጳጉሜን ጽንሰ ሃሳብ ግን ቅድስተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ሂደህ የበሐረ ሃሳብ ሊቃዉንቶችን ማነጋገር ትችላለህ ሲሉ ጠቆሙኝ፡፡ በጥቆማቸዉመሰረት ሊቃዉንቶቹ የሚገኙበት ቦታ ካንዴም ሁለቴ በመሄድ ጳጉሜን ጠየኳቸዉ፡፡ ከዚያም ሁለት ነገሮችን አገኘሁ፡፡ (1ኛ) ከላይ የተመለከተዉን አምስተኛ ተድጋሮት መኖሩን እና (2ኛ) የጳጉሜን ጽንሰ ሃሳብ የሚመለከት ዘመናዊ መጸሐፍ እጅግ አጥብቄ እንድፈልግና እንዳገኝ አቅጣጫ ሰጠኝ፡፡

 

በመሆኑም ግሬስዴል (1956 አ.ዶ) የተሰኘዉ እንግሊዛዊ የመልካ ምድር ሳይንቲስት አመካይ የፀሃይ ዓመት ማለት 365.25 እለት የያዘ ጊዜ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ለተከታታይ ሦስት ዓመት 365 እለት እና በአራት ዓመት አንዴ ጳጉሜ 6 ላይ የእምርታ ዓመት ሁኖ መለወጡን የፃፈዉ የእነርሱ ከሚለወጥበት ፌብሩዋሪ 29 የተለየ መሆኑን በማነፃፀር ጭምር ነዉ፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያ ለምድር ወገብ ቅርብ ስለሆነች የ12 ሰዓት ቀን እና 12 ሰዓት ለሊት ጊዜ ስርኣት ቀን መቁጠሪያ መጠቀሟ ተገቢ መሆኑን ከማረጋገጡም በላይ እዚህ እኛ ጋር የሚከሰቱትን መካከለኛ ወቅቶች እነርሱጋር በሚከሰቱት ከፍተኛ ወቅቶች  ( ክረምትን በሰመር እና በጋን በዊንተር) በዉርስ ተተረጉመዉ መገኘታቸዉ እጅግ አስከፊ ስህተት ስለሆነ መታረም እንደሚገባዉ ግሬስዴል መክሮ ነበር፡፡ ስለዚህ ግሬስዴል ጳጉሜ 6ን እና ፌብሩዋሪ 29ን ከማነፃፀሩም በላይ የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ማለት የ12 ሰዓት ቀን እና 12 ሰዓት ለሊት ጊዜ ስርዓት እና  በሞቃት ምድር ዉሥጥ  የሚከሰቱትን መካከለኛ ወቅቶች  የሚያሳይ ማለት መሆኑን የሚጠቁም መነሻ ፍንጭ እንድናገኝ እጅግ ከፍተኛ አስተወፆ ማድረጉን መጠቆም እወዳለሁ፡፡ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ድረስ የተመለከቱትን  ሦሥት መሰረታዊ ተግዳሮቶች በሂደት ያስተዋልኩት የመጀመሪያዉን ተግዳሮት ከ17 ዓመት በፊት ከተገነዘብኩበት ጊዜ ጀምሮ፤ ችግሩን መቀረፍ አለብን እያልኩ  በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከማስተማር ጎን ለጎን የዉትወታ መጣጥፎች በየጊዜዉ እየሰራሁ ለጥናት ታዳሚያዎች አቀርብ ስለነበር ጭምር ነዉ፡፡

 

ስለዚህ ጳጉሜ 6 የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ የማን ነዉ የተሰኘዉን መጽሐፍ የፈጠረኩት በአራት የጊዜ ማስረጃዎች፤ በምልከታ እና በአዲስ የጊዜ አጠናን ዘዴ በመታገዝ ነዉ፡፡  ማስረጃ አንድ ማለት የዓመተ ምህረት እና አኖ ዶሚኒ ቁጥሮችን የሚመለከት ማስረጃ ሲሆን (የኢትዮጵያን ቀን መቁጠሪያ ከግሪጎሪያን ቀን መቁጠሪያ አንፃር ያለዉን ልዩነተ ለማሳየት ) ከመቁጠሪያዉ ላይ የ68 ዓመታት (ከ1933 እስከ 1999 ዓ.ም እና ከ1940 እስከ 2006 አ.ዶ) የተወሰደ ነዉ፡፡ ማስረጃ ሁለት  በአመት ዉስጥ በምሥራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃት ምድር ዉስጥ  የሚከሰቱ አራት መካከለኛ ተቃራኒ ወቅቶች መለወጫ  የወር እለቶች ሰኔ 14 ማብቂያ፤ መስከረም 13፤ ታህሳስ 12፤ መጋቢት 12 እና ሰኔ 14 መሆናቸዉን  እና በጠባብ ቀዝቃዛ ምድር ዉስጥ የአራቱ ከፍተኛ ተቃራኒ ወቅቶች መለወጫ አምስት  እጅግ ረጅምና አጭር የቀን ወር እለቶች ጁን 14 ማብቂያ፤ ሰብቴምበር 23፤ ደሴምበር 21፤ ማረች 21 እና ጁን 21 መሆናቸዉን የሚመለከት ማስረጃ ነዉ፡፡ ማስረጃ ሦሥት አጭር የቀን ሰዓት ቁጥሮች ከምሥራቅ ሰሜን ሞቃት ምድር ድንበር ቦታዎች እና ረጅም የቀን ሰዓት ቁጥሮች ከቀዝቃዛ ምድር ድንበር ቦታዎች ላይ መመዝገባቸዉን ከሚያሳየዉ መረጃ መረብ ላይ የተወሰዱ ናቸዉ፡፡ ማስረጃ አራት የኢትዮጵያ 12ቱ ወሮች እና የግሪጎሪያን 12 ወሮች ማለት ሲሆኑ፤ በመደበኛ ዓመት (የባለ 365 እለት) እና እምርታ ዓመት (የባለ 366 እለት) ዉሥጥ የሚከሰቱት 12፤ 12 ወሮች ከየመቁጠሪያዎቹ ላይ የተወሰዱ ናቸዉ፡፡ የጳጉሜ 6 መጽሐፍ አጠናን ዘዴ እጅግ ቀላል እና አዲስ ነዉ፡፡ የአጠናን ዘዴዉ እጅግ ቀላል ዘዴ ነዉ ማለት በኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ወሮች ቅደም ተከተል መሰረት እያንዳንዱን ወር ከግሪጎሪያን እያንዳንዱ ወር ጋር በዘመናዊ የኮምፒዉተር ኤክሴል ማነፃፀር፤ በምሥራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃት ምድር ዉሥጥ የሚከሰቱትን አራት መካከለኛ ተቃራኒ ወቅቶችና አጭር የቀን ልዩነት በሰሜንና ደቡብ  ጠባብ ቀዝቃዛ ምድር ዉስጥ ከሚከሰቱት አራት ከፍተኛ ተቃራኒ ወቅቶችና ረጅም ቀን ልዩነት ፍፁም የተለዩ መሆናቸዉ በአንፃራዊ ጊዜ አጠናን ዘዴ የተሰራ ነዉ፡፡ የዘመናዊ ጊዜ አጠናን ዘዴ አዲስ ነዉ ማለት ከዚህ በፊት የሞቃት ምድር ጊዜ እና የቀዝቃዛ ምድር ጊዜ ተለይተዉ የተፈጠሩ መሆናቸዉን በሚመለከት ከሁለት ቀን መቁጠሪያ ወሮች፤ መካከለኛ እና ከፍተኛ ወቅቶች ክስተት እና ረጅም እና አጭር ቀን ሰዓት ፍሰት መረጃዎችን እያነፃፀረ  ያጠና ሰዉ ባለመኖሩ ነዉ፡፡

በመሆኑም በጳጉሜ 6 መጽሐፍ ይዤ የመጣሁት ዋና ዋና አምስት ግኝቶችን ነዉ ፡፡

 • የሶስት ምድብ አራት ዓመት ዘላለማዊ ሰኝጠረዞች፤ በሦስት ምድብ አራት ዓመት ሰንጠረዥ መረጃ ስር ደግሞ ሦስት ተጨማሪ ግኝቶች የሶስት ምድብ አራት ዓመተ ምህረት ቁጥሮች፤ የጋራ እና ልዩነት ወር እለቶች እና የጳጉሜ 5 እና 6 እለቶች ከሰብቴምበር 6 እስከ 10ና 11 አንፃር ተለይተዉ የታወቁ መሆናቸዉን ነዉ፡፡
 • የምስራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃት ምድር ዉሥጥ በየዓመቱ የሚከሰቱት አራት መካከለኛ ተቃራኒ ወቅቶች፡-ክረምት እና በጋ፤ መፀዉ እና ፀደይ፤ በጋ እና ክረምት እና ፀደይ እና መፀዉ ሲሰኙ፤ በምሥራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ጠባብ ቀዝቃዛና ቀርፋፋ ምድር ዉሥጥ የሚከሰቱት አራት ከፍተኛ ተቃራኒ ወቅቶች፡-ሰመር እና ዊንተር፤ አዉተመን እና ስብሪንግ፤ ዊነተር እና ሰመር እና ስፕሪንግ እና አዉተመን መሰኘታቸዉን፤
 • የሞቃት ምድር አጭር የቀን አማካይ እለት ከቀዝቃዛ ምድር ረጅም አማካይ እለት መለየቱን፤
 • የኢትዮጵያን 12 ወሮች ስም እና የግሪጎሪያኑን 12 ወሮች ስም እንዲሁም የእያንዳንዳቸዉን ወር ቁጥር በመደበኛ እና ልዩ ዓመት በዘመናዊ የኤከሴል ነጠላ ሰኝጠረዥ ዉሥት በማጎር እና በማቀናነስ  ጳጉሜን በመደበኛ ዓመት 5 እለት እና በእምርታ ዓመት 6 እለት መሆኑን በመፍጠር
 • ጰጉሜ ማለት የሞቃት ምድር 5 እና 6  ፈጣን ሹረት ማለት ሲሆን፤ ከሰብቴምበር 6 እስከ 10ና 11 እለት ማለት ግን የቀዝቃዛ ምድር 5ና 6  ቀርፋፋ ሹረት ማለት ነዉ የሚል ነዉ፡፡

ነገር ግን ከላይ የተገለፀዉን አዲስ ጭብጥ ተከትሎ ተከታታይ የተቀዉሞ እና የተቃዉሞ ማፍረሻ መጣጥፎች በአዲስ አድማስ ሳምንታዊ ጋዜጣ ላይ በመቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም  ጳጉሜ 6 ስለየትኛዉ ዘመን መቁጠሪያ ነዉ የሚናገረዉ በሚል የመጀመሪያ ተቃዉሞ ጥቅምት 23፤2006 ዓ.ም ቀርቦ ነበር፡፡ የጳጉሜ 6ን ተቃዉሞ ማፍረሻ ሐምሌ 25፤2007 ዓ.ም መስጠቴን ተከትሎ ፤ ሁለተኛ ተቃዉሞ እመቤቴ ሆይ ጳጉሜ የዘመን ቆጠራችን ጉዳይ በሚል ርእስ ነሐሴ 23፤2007 ዓ.ም እና መስከረም 1፤2008 ዓ.ም በተከታታይ ቀርቦ ይገኛል፡፡

 

ሆኖም ግን በጳጉሜ 6 ላይ እየቀረቡ የሚገኙት የተቃዉሞ መጣጥፎች በኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ እና ግሪጎሪያን ካሌንደር ላይ ለይብቻ በመመዝገብ ላይ የሚገኙትን ወሮች በማነፃፀር የተገኙትን አዲስ ጭብጦች አይቃወሙም፡፡ ጳጉሜ ማለት  የሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃት ምድር 5 እና 6 ፈጣን ሼረት ከሰብቴምበር 6 እሰከ 10ና 11 ድረስ ከሚገኘዉ ቀርፋፋ ሹረት ፍፁም ተለይቶ መፈጠሩን አልተቃወሙም፡፡ በመሆኑም በጳጉሜ ዉስጥ ደመወዝ ለሰራተኛ፤ የቤት ኪራይ ገቢ ቤት ሰርቶ ላከራየ፤ የገንዘብ ቁጠባ ወለድ፤ ገንዘቡን ባንክ ለቆጠበ ወዘተ ብቻ ሳይሆን ለመንግስትም ተጓዳኝ የገቢ ግብር ጭምር መፍጠር አለብን ከሚለዉ የመፍትሄ ጭብጥ ላይ ተቃዉሞ አላቀረቡም ፡፡ ከዚያም በላይ የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ የኛ ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃት ምድር ዉስጥ የሚገኙ አገሮች ጭምር ሰለሆነ ተቀብለዉ እንዲጠቀሙበት በማድረግ በቅኝ አገዛዝ እና በእነርሱ ጠባብ ቀዝቃዛ ምድር ላይ በተሰራዉ ዘመናዊ ትምህርት አማካይነት ካለ ጊዜ ተፈጥሮ በሞቃት ምድር ዉሥጥ ገብቶ የሚገኘዉን የግሪጎሪያን ቀን መቁጠሪያ ወደ መጣበት በመመለስ የኢተዮጵያን አፍሪካ ህዳሴ አዲስ አለም ፈጠራ ማቀላጠፍ አለብን ከሚለዉ  የእዉነት  መፍትሄ ጋርም ጥል የላቸዉም፡፡ ስለዚህ በጳጉሜ 6 ላይ እየቀረበ የሚገኘዉ ተቃዉሞ ምንጭ ምንድን ነዉ? አስከፊ ጭብጦቹ እና አንድምታዉ ምንድን ናቸዉ የሚሉትን ጥያቄዎች እንደሚከተለዉ መፈተሽ እወዳለሁ፡፡

 • የተቃዉሞምንጮች ፤ አስከፊ ጭብጦች እና አንድምታዎች

ሀ.የተቃዉሞምንጮች

የጳጉሜ 6 ተቃዉሞ ምንጭ ተቃዋሚዎቹ የተመሰረቱበት ሦሥት የተሳሳቱ መረጃዎችእና ሦሥት ሳይንሳዊ እዉቀትና ክህሎት እጦት ናቸዉ፡፡ተቃዋሚዎቹ የተመሰረቱበት ሦሥት የተሳሳቱ ምንጮች፡-

 • አቡሻኽር በተሰኘዉ ጥንታዊ አስተምህሮት ዘዴ የኢትዮጵያ አቆጣጠር በሚል የተማሩት እና የሚያስተምሩት የጊዜ ንድፈ ሃሳብ በቀጥታ ከጥንታዊ ጁሊያን አቆጣጠር ላይ በዉርስ የተተረጎመ መሆኑ ነዉ፡፡
 • የግሪጎሪያን አቆጣጠር ከኦክቶበር5፤1582 አ.ዶ ጀምሮ ያሳሳተዉን አማካይ የፀሃይ ዓመት 365 እለት፤ 5 ሰዓት፤ 48 ደቂቃ አነ 46 ሰከንድ ትክክል ነዉ ብለዉ መቀበላቸዉ ነዉ፡፡
 • ጳጉሜ 6 በመፀሐፈ ሄኖክ አይታወቅም፡፡

እንዲሁም ተቃዋሚዎቹ ሦሥት ሳይንሳዊ የፀሃይ ዓመት ጭብጦችን አያዉቁም፡፡

 • ምድር በየ24 ሰዓት እየፈጠነችና እየተንቀረፈፈች በመሾር ፀሃይን በየ365.25 እለት በመዞሩ የተነሳ የፀሃይ ዓመት መባሉን ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ ምእራብ ሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃትና ፈጣን ምድር ዉሥጥ ወደ መሬት ማዉረጃዉ  የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ከረቡእለት፤ መስከረም 1፤ 5500 አመተ ፍዳ ላይ ጀምሮ እስከ ሰኞእለት፤ ጳጉሜ 6፤ 6019 ዓ.ፍ ማገልገሉን ብቻ ሳይሆን ከማከስኞእለት፤ መስከረም 1፤ 0 ዓ.ም ጀምሮ አሁን እየተገለገልንበት መሆኑን ፍፁም አላወቁም፡፡ በመሆኑም መነሻቸዉ እጅግ ዘግይቶ 46 ቅ.ክ ላይ ያሰሩትና ቱስዴይ፤ ሰብቴምበር 12፤07 አ.ዶ ላይ የጀመረዉ የጁሊያን መቁጠሪያ ነዉ፡፡

 

 • በእንገሊዘኛ አማርኛ መዛግብተ ቃላት ኤፕሪልን ሚያዝያ፤ ኦገስትን ነሃሴ ወዘተ እና ሰብቴምበርን መስከረም ብለዉ ካለ ጊዜ አገባብ በዉርስ ተርጉመዉ ጳጉሜ የተሰወረባቸዉን ይቀበላሉ፤ የግዕዝ ሳምንት የእለት ትርጉም ባለመያዛቸዉ የተነሳ በእንግሊዘኛ ሳምንት በዉርስ ተተርጉመዉ መገኘታቸዉን ይቀበላሉ፡፡

 

 • የአንፃራዊ ወቅት አጠናን ዘዴ የቀን ሰዓት የእለት ጥገኛ መሆኑን የሚያሳየዉን የሥነ ሂሳብ ቋንቋ እና የአማርኛ ቋንቋ አልታጠቁም፡፡

እንዲሁም የጳጉሜ 6 መጽሐፍ በኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ዓመተ ምህረት እና በጁሊያኑ በሁዋላም ግሪጎሪያን ቀን መቁጠሪያ አኖ ዶሚኒ መካከል የሚታየዉን ልዩነት ምክንያት አለመካተቱ ለተቃዋሚዎቹ ተመችቶ ነበር፡፡  ስለሆነም በስህተት መረጃ ላይ ተመስርተዉ እና ካለዘመናዊ የጊዜ እዉቀትና ክህሎት በበጳጉሜ 6 ላይ እየቀረቡ የሚገኙት የተቃዉሞ መጣጥፎች እጅግ አስከፊ ጭብጦች ናቸዉ፡፡

ለ. እጅግ አስከፊ ጭብጦች

በጳጉሜ 6 ላይ አራት እጅግ አስከከፊ የሃሰት ተቃዉሞ ጭብጦች ቀርበዋል፡፡

 • አሁን ኢትዮጵያ የምትጠቀመዉ የዘመን አቆጣጠር ከጁሊያን ቀን መቁጠሪያ ጋር አንድ  መሆኑ ምንም አያሳፍር፤
 • ጳጉሜ 6 በየ600 ዓመት 7 ሊሆን ይችላል፤
 • እንደ አዉሮፓ አቆጣጠር በመጪዉ ጥር የኢየሱስ ክርስቶስ እድሜ 2023 ሲሆን እነርሱ በ7 ዓመት እኛ ደግሞ በ15 ዓመት ተሳስተናል፤
 • የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ማስተካከያ ሊደረግበት ይገባል የሚሉ ናቸዉ፡፡እነኝህ እጅግ አስከፊ ጭብጦች አሉታዊና አወንታዊ አንድምታ አላቸዉ፡፡

ሐ. አሉታዊ አንድምታ

አሉታዊ አንድምታዉ በኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ላይ ብቻ ሳይሆን በሁለንታዊ የሂሳብ ቋንቋ እና ሁለንታዊ የአማርኛ ቋንቋ ላይ  የተቃጡ ተፃራሪ ዉሸት ማስቀጠያ ሙከራዎች መሆናቸዉ ነዉ፡፡

መ. አወንታዊ አንድምታ

 

በጳጉሜ 6 ላይ የቀረቡት ተቃዉሞዎች ሦሥት አወንታዊ አንድምታ አላቸዉ፡፡

 • እየቀረቡ የሚገኙት ተቃዉሞዎች በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ከስራ ዉጭ ከሆነዉ ጥንታዊ የጁሊያን ካሌንደር ጋር አንድ አይነት ነበር የሚሉ ሰዎች አሁን በግሪጎሪያን ካሌንደር አስተክተዉት የሚገኙ መሆናቸዉን እንድናዉቅ ማድረጉ፤

 

 • እመቤቴ ሆይ ጳጉሜን የዘመን ቆጠራችንጉዳይ ጉዳይ ሲሉ ሁለተኛዉ ተቃዋሚ ያቀረቡት የመሟገቻ ርዕስ የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ዓመተ ምህረት ሰኞእለት፤ ጳጉሜ 6፤ 6019 ዓ.ፍ እንደተፈፀመ ፀሃይ ብልጭ ስትል አዲስ በቀጠለዉ  ማክሰኞእለት፤ መስከረም 1፤0 ዓ.ም ላይ እየሱስ ክርስቶስ ከተወለደበት ቅጽበት ላይ መጀመሩን እንድናዉቅ ብቻ ሳይሆን  የምዕራብ ሰሜን ጠባብ ቀዝቃዛ ምድር ሰዎች ቱስዴይ፤ ሰብቴምበር 12፤ 7 አ.ዶ ብለዉ መጀመራቸዉን በአንፃራዊ የጊዜ ምርምር እንድናዉቅ አድርጉል፡፡

 

 • በእኔ እና በሁለት የጥንታዊ ባሕረ ሓሳብ ሰዎች ካከል ለተከታታይ ሦሥት ዓመት (1ኛ ጥቅምት 23፤2006 ዓ.ም ፤2ኛ ሐምሌ 25፤2007 ዓ.ም ፤ 3ኛ ሁለተኛ ተቃዉሞ  ነሐሴ 23፤2007 ዓ.ም እና መስከረም 1፤2008 ዓ.ም እና 4ኛ ነሃሴ 6፤2009 ዓ.ም) በአዲስ አድማስ ሳምንታዊ ጋዜጣ ላይ ያደረግናቸዉ እሰጣ ገባዎች ፤ ከ18 ዓመታት በፊት የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ ገቢ ግብር ሂሳብ አሰራር እና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያስከተለዉ ተጽእኖ በሚል ርዕስ ያበረከትኩትን አዲስ የግብር ሂሳብ እዉቀትና ክህሎት ተከትሎ፤በተመሰከረለት ከፍተኛ ሂሳብ ባለሙያ እና ሌላ የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የገቢ ግብር ሰንጠረዥ አርቃቂ ኢኮኖሚስት መካከል ለተከታታይ ሦሥት ዓመታት (ከጥር 1991 እስከ መስከረም፤ 1994 ዓ.ም) በልሳነ ኢኮኖሚክስ ላይ አድርገናቸዉ ከነበሩት እሰጣ ገባዎች ጋር ተመሳሳይ ከመሆናቸዉም በላይ  አዲስ አድማስ የቀደደ የጊዜ እዉቀት ፈጠራ እጅግ ረጅም ዓመታት መዉሰዱን ማሳየት ስለቻለ የተቃዉሞ ዋንኛ አወንታዊ ጎን አድርገን ወስደነዋል፡፡

 

 • የዚህ መጣጥፉ አላማ እና ዝርዝር ግቦች
  • አላማ

የመጣጥፉ አላማ በጳጉሜ 6 (በኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ) ላይ ለሁለተኛ ጊዜ እመቤቴ ሆይ ጳጉሜ የዘመን ቆጠራችን ጉዳይ በሚል ርእስ ነሐሴ 23፤2007 ዓ.ም እና መስከረም 1፤2008 ዓ.ም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ቀርቦ የነበረዉን ተቃዉሞ ከምንጩ በማፈራረስ ወደ ተግባር መግባት እንዳለብን ማስገንዘብ ነዉ፡፡

 • ዝርዝር ግቦች

ዝርዝር ግቦቹ(1ኛ) የግዝን ሳምንት እንግሊዘኛ ሳምንት ዉርስ ትርጉም የሚሽረዉን የአማርኛ ሳምንት የምንፈጥረዉ እንዴት ነዉ? (2ኛ) ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደዉ መቼ ነዉ? (3ኛ) የጁሊያን መቁጠሪያ ከ7 ዓመት አመት በላይ አሳስቶ የጀመረዉ ለምንድን ነዉ? (4ኛ) በግሪጎሪያን መቁጠሪያ የተሰሩት አራት ተጨማሪ ቅሌቶች ምንድን ናቸዉ?  ለሚሉት ጥያቄዎች እጅግ ሳይንሳዊ መልሶችን በማበርከት የጳጉሜ 6ን አጠናን እና አተገባበር ዘዴ ለህዝብ ይፋ ማድረግ ናቸዉ፡፡

2. የመቁጠሪያ ጥናት ቤተሙከራ፤የሳምንት ፈጠራ እና ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደ ዉመቼ ነዉ?

2.1. የቀን መቁጠሪያ አጠናን ቤተ ሙከራ

የኢትዮጵያን ቀን መቁጠሪያ በሚመለከት ጥናት የሚያደርግ ሰዉ ቤተ ሙከራዉ የምሥራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃትና ፈጣን ምድረ ሰማይ ሲሆን፤ ቀደም ሲል የጁሊያን አሁን የግሪጎሪያን ስለሚባለዉ ቀን መቁጠሪያ የሚያጠና ሰዉ ቤተ ሙከራዉ የምሥራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ጠባብ ቀዝቃዛና ቀርፋፋ ምድረ ሰማይ ነዉ፡፡

2.2. የአማርኛ ሳምንት ፈጠራ

የኢትዮጵያን ቀን መቁጠሪያ በምሠራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃትና ፈጣን ምድር ዉስጥ ስራ ላይ ማዋል የተፈጥሮ ህግጋት ነዉ፡፡ ምክንያቱም በመቁጠሪያዉ ላይ ይመዘገቡ የነበሩት፤ እየተመዘገቡ የሚገኙት እና ወደፊት የሚመዘገቡት  ፈጣን ወሮች እና የሶሥት ምድብ አራት ዓመተ ምህረቶች የሞቃት ምድር ናቸዉ፡፡ ነገር ግን በመቁጠሪያዉ ላይ እየተመዘገቡ የሚገኙት የግእዝ ሳምንት፡-ሰኞ፤ ማክሰኞ፤ ረቡ፤ ሃሙስ፤ አርብ፤ ቅዳሜ እና እሁድ  የምሥራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃት ምድርን እለት (24 ሰዓት፤ 12 ሰዓት ቀን እና 12 ሰዓት ሊለት) ትርጉም ካለመያዛቸዉም በላይ ሰኞ እና ማክሰኞ፤ ሞኞ ከምንለዉ ሌላ የአማረኛ ቃላ ጋር ይመሳሰላሉ፡፡ ሞኝ ማለት ደግሞ ጅል፤ ቂል፤ የሚታለልና ምንም የማያዉቅ የሚል ፍች ይዞ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የግእዝ ሳምንት ለእንግሊዘኛ ሳምንት ዉርስ ትርጉም ተጋልጠዉ ይገኛል፡፡ ነገር ግን በግሪጎሪያን መቁጠሪያ ላይ ከመንዴይ እስከ ሰንዴይ ሁነዉ እየተመዘገቡ የሚገኙት የሳምንት ስሞች የእንግሊዘኛ ሳምንት ይባላሉ፡፡ የእንግሊዘኛ ሳምንት የተባሉበት ምክንያት እንግሊዞች የሰሜንና ደቡብ ጠባብ ቀዝቃዛ ምድርን 24 ሰዓት ማሳየት እንዲችሉ፤ በጁሊያን ሳምንት ስሞች ላይ ዴይ ( ዳይ ላይት-ቀን እና ናይት-ለሊት) የሚል ቃል ጨምረዉ ወደ ተግባር በማዞራቸዉ እና ከ1752 አ.ዶ ጀምሮ ዘመናዊ ትምህርት ዉስጥ በማካተታቸዉ ነዉ፡፡

 

እኛም የኢትዮጵያን አፍሪካ ህዳሴ ረቡእለት፤ መስከረም 1፤ 2000 ዓ.ም. ላይ የጀመርነዉ፤ የጨለማዉን ዘመን ማክሰኞእለት፤ ጳጉሜ 6፤1999 ዓ.ም ባበቃበት ቅጽበት ላይ ጨርሰን መሆኑ ይታወሳል፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ አፍሪካ ህዳሴ  አዲስ አለም የመፍጠር ጥንሥስ በአፍሪካ ሕብረት ጭምር የታወጀዉ በመቁጠሪያችን ነዉ፡፡ ቀሪዉ ስራ ወደ ተግባር ማዞር ነዉ፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ አፍሪካ ህዳሴ ዘመን ዉስጥ በሞኝነት መቀጠል ስለማይቻል ብቻ ሳይሆን ፣ የምሥራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃት ምድር 24 ሰዓት ጊዜ ትርጉም በመፍጠር የዉረስ ትርጉምን ለመሻር እና የአፍሪካን ህብረት መሪዎች ዉሳኔ  ወደተግባር በቀላሉ መለወጥ እንድንችል፤ የግእዝን ሳምንት ወደ አማርኛ ሳምንት (ከእንግሊዘኛ ሳምንት አንፃር) መለወጥ ሳይንሳዊና ተፈጠሮያዊ ሁኖ ተገኝቷል፡፡ በመሆኑም የአማርኛ ሳምንት ማለት ሰኞእለት(Segnoelt)፤ ማክሰኞእለት (Maksegnoelt)፤ ረቡዕለት(Robelt)፤ ሃሙስእለት(Hamuselt)፤ አርብእለት (Arbelt)፤ ቅዳሜእለት(Kidamelt) እና እሁድእለት (Ehudelt) ናቸዉ፡፡ ትርጉማቸዉም በሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃትና ፈጣን ምድር ዉስጥ የሚከሰቱ 7 ተከታታይ እለቶች ማለት ነዉ፡፡ የእንግሊዘኛ ሳምንት ማለት መንዴይ፤ ቱስዴይ፤ ዊድንስዴይ፤ ተርስዴይ፤ ፍራይዴይ፤ ሳተርዴይ እና ሰንዴይ ሲሆኑ፤ በሰሜንና ደቡብ ጠባብ ቀዝቃዛና ቀርፋፋ ምድር ዉስጥ የሚከሰቱ 7 ተከታታይ እለቶች ማለት ናቸዉ፡፡

2.2.         ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደዉ መቼ ነዉ?

አቶ አብነት ስሜ፤ እንደ አዉሮፓ አቆጣጠር በመጪዉ ጥር የኢየሱስ ክርስቶስ እድሜ 2023  ሲሆን እነርሱ በ7 ዓመት እኛ ደግሞ በ15 ዓመት ስለተሳሳትን የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ማስተካከያ ሊደረግበት ይገባል ሲሉ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ የቻሉት የምዕራብ ሰሜን ጠባብ ቀዝቃዛ ምድር ሰዎች ስለ ጁሊያን መቁጠሪያ አሳስተዉ ፅፈዉት ከነበረዉ ላይ  በዉርስ የተተርጉመ መረጃ ተጠቅመዉ መሆኑን እንደሚከተለዉ ማወቅ ተችሏል፡፡

"… ዘመን ቆጠራ የጀመሩት ማክሰኞ ቀን ነዉ፡፡ እኛም ከዚያ ማክሰኞ፤ መስከረም 1፤ 5500 ቅድመ ክርስቶስ ተነስተን ነዉ የምንቆጥረዉ፡፡"ፕሮሴፈር ጌታቸዉ ኃይሌ (2006፡50)

ነገር ግን ፕሮፌሰሩ እኛም ከዚያ ማክሰኞ፤ መስከረም 1፤ 5500 ቅድመ ክርስቶስ ተነስተን ነዉ የምንቆጥረዉ ያሉት ሃሳብ በዉርስ የተተረጎመ ስለሆነ የኢትዮጵያን ቀን መቁጠሪያ አይመለከትም፡፡ በመሆኑም ማክሰኞ የተሰኘዉ የግእዝ ሳምንት ስም በአማርኛ ማክሰኞእለት በሚል ተፅፎ ቢሆን ኖሮ 24 ሰዓት ትርጉም ማሳየት ይችል ነበር፡፡ እንዲሁም የመስከረም ወር ክረምቱ ስላበቃ መስክ ወጥተህ/ወጥተሽ ስትሰራ/ስትሰሪ ክረም/ክረሚ የሚል የተፈጥሮ ምልከታ እና ድርጊት ትርጉም ይዞ ጥንት ዓመተ ፍዳ ዉሰጥ መፈጠሩ መታወቅ ነበረበት፡፡ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ አመተ ፍዳ በእነርሱ ቅድመ ክርስቶስ በዉርስ መተርጎም አለመቻሉ መታወቅ ነበረበት፡፡ ምክንያቱም ዓመተ ፍዳ ዓመት እና ፍዳ ከተሰኙት ሁለት የአማርኛ ቃላቶች ተወስዶ የተሰራ ሲሆን፤ ዓመት ማለት ምድር በየ24 ሰዓት እየፈጠነችና እየተንቀረፈፈች በመሾር ፀሃይ ለመዞር የሚወስድባት ጊዜ 365.25 እለት መሆኑን ብቻ ሳይሆን ይህንኑ ወደ መሬት ማዉረጃዉ የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ በሦሥት ምድብ አራት ዓመት ጥንት ከረቡእለት፤ መስከረም 1፤5500 ዓ.ፍ ላይ የተሰራና የጀመረ መሆኑን የሚያሳይ ስለሆነ ነዉ፡፡ ፍዳ ማለት ግን እዉቀት፤ ትምህርት የሌለበትና ችግር፤ ስቃይና ድንቁርና የበዛበት ማለት ነዉ፡፡ አሁን ግን መስከረም 1፤ 5500 አ.ፍ የዋለዉ ማክሰኞእለት ላይ ሳይሆን ረቡእለት ላይ እንደነበር ማወቅ ችለናል፡፡ ስለዚህ መስከረም 1 ማክሰኞእለት ላይ ዉሎ የነበረዉ በ5488 አ.ፍ ላይ ነበር ማለት ነዉ፡፡ስለሆነም ረቡእለት፤ መስከረም 1፤ 5500 አ.ፍ እንደተፈፀመ ፀሃይ ብልጭ ስትል ሐሙስእለት፤ መስከረም 2፤ 5500 አ.ፍ ቀጥሎ ስለነበር እየሱስ ክርስቶስ ገና አለመወለዱ በፕሮፌሰሩ መታወቅ ነበረበት፡፡

 

ስለዚህ እየሱስ ክርስቶስ የተወለደዉ መቼ ነበር የሚለዉ ጥያቄ መልስ ቀጥሎ በተመለከተዉ ሁለተኛ የዉርስ ትርጉም ዉስጥ መገኘቱን ወይም አለመገኘቱን መፈተሸ አስፈላጊ ነዉ፡፡

" በኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት፤እነዲሁም … ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ከድንግል ማርያም የተወለደበት ጊዜ፡ በጳጉሜ 5 ቀን ፡5500 ዓመተ ዓለም ከለሊቱ 6 ሰዓት ሞልቶ፡ አንዲት ካልዕት ለማትሞላ አፍታ፡ጥቂት እልፍ ብላ በነበረችው ቅጽበት ውስጥ መሆኑ ነው፡፡መስከረም 1 ቀን፤ 1 ዓመተ ምህረት ተብሎ የዓመተ ምህረት ዘመን አቆጣጠር የጀመረው በዚያች፡ የዓመተ ኩነኔ፡ ወይም የዓመተ ፍዳ ማብቂያ ከሆነችው፡ጳጉሜ 5 ቀን ፡5500 ዓመተ ዓለም፡ ከለሊቱ 6 ሰዓት በኋላ ከነበረችው ቅጽበት ጀምሮ ኾኗል፡፡" ንቡረ እድ ኤርሚያስ ከበደ ወልደ ኢየሱስ (1997፡306)፡፡

በኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት … እየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም የተወለደበት ጊዜ የሚለዉ ሃሳብ እጅግ የሚያስመሰግን ቢሆንም፤ እርሱ የተወለደበት ጊዜ ጳጉሜ 5 ቀን ፡5500 ዓመተ ዓለም  ከለሊቱ 6 ሰዓት ሞልቶ፡ አንዲት ካልዕት ለማትሞላ አፍታ፡ጥቂት እልፍ ብላ በነበረችው ቅጽበት ውስጥ ስለነበር፤ ከዚያ ጀምሮ መስከረም 1 ቀን፤ 1 ዓመተ ምህረት ተብሎ የዓመተ ምህረት ዘመን አቆጣጠር ተጀመረ የሚለዉ ሃሳብ ጳጉሜ 6ን ወይም የኢትዮጵያን ቀን መቁጠሪያ ስርዓት በሦሥት ምክንያት አይመለከትም፡፡

 • የኢትዮጵያ ቀን አቆጣጠር ስርዓት ከምሥራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃትና ፈጣን ምድረ ሰማይ ላይ ይቀዳ የነበረ፤ በመቀዳት ላይ የሚገኝ እና ወደፊት የሚቀዳ የተፈጥሮ ጊዜ ስርዓት መዝገብ መሆኑ አልታወቀም፡፡

 

 • የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪ አቆጣጠር ስርዓት እኩለ ለሊት 6 ሰዓት ማብቂያ ቅጽበት ላይ ሳይሆን ለሊቱ 12 ሰዓት ሞልቶ ሲያበቃ ፀሃይ ብልጭ ካለችበት ቅጽበት ላይ የሚጀምር ስርዓት ነዉ፡፡ በመሆኑም አቆጣጠሩ ፀሃይ ብልጭ ብላ እስክትጠልቅ ድረስ የሚታየዉን የብርሃን ጊዜ 12 ሰዓት ቀን እና  ፀሃይ ጥልቅ ብላ ተመልሳ ብልጭ እስክትል ድረስ ብርሃን የማይታይበት የጨለማ ጊዜ 12 ሰዓት ለሊት አድርጎ የሚጠቀም ተፈጥሮያዊ እና እጅግ ዘመናዊ የጊዜ ስርዓት መሆኑ ከግንዛቤ መግባት ነበረበት፡፡

 

 • ረቡእለት፤ ጳጉሜ 5፤ 5500 ዓ.ፍ ዉሎ እንደተፈፀመ፤ ጠዋት ፀሃይ ብልጭ ስትል ሃሙስእለት፤ መስከረም 1፤5501 ዓ.ፍ የጀመረዉ አዲስ ዓመት የምድብ ሁለት የመጀመሪያዉ አመተ ፍዳ ነበረ፡፡ በመሆኑም ሃሙስእለት፤ መስከረም 1፤5501 ዓ.ፍ ቀጥሎ ስለነበር ገና እርሱ ባለመወለዱ የተነሳ የዓመተ ምህረት አቆጣጠር አለመጀመሩ መታወቅ ነበረበት፡፡

በመሆኑም እየሱስ ክርስቶስ የተወለደዉ መቼ ነበር የሚለዉ ጥያቄ በጥንታዊያኖች  የዉርስ ትርጉም ዉስጥ መገኘት አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ከላይ በተከታታይ በተመለከትናቸዉ ሁለት የዉርስ ትርጉም መሰረት  እርሱ ገና አልተወለደም፡፡ ስለሆነም መልሱ የሚገኘዉ በአመተ ምህረት በመቁጠሪያችን ላይ ነዉ፡፡ዓመተ ምህረት ማለት እየሱስ ክርስቶስ ከተወለደበት አፍታ ጀምሮ በኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ላይ ይመዘገብ የነበረ፤ እየተመዘገበ የሚገኝ እና ወደፊት የሚመዘገብ ፈጣን የሦሥት ምድብ አራት ዓመት መኖሩን የሚያሳይ የጊዜ ጽንሰ ሃሳብ ሲሆን፤ ከአማርኛ ሁለት ቃላቶች አመት እና ምህረት ተወስዶ የተሰራ ነዉ፡፡ በመሆኑም አመት ማለት ከላይ በተተረጎመዉ መሰረት አማካይ የፀሃይ ዓመት 365.25  እለት የያዘ ጊዜ ማለት ሲሆን፤ ምህረት ማለት  ድንቁርና፤ ስቃይ እና ፍዳ የሌለበት በምህረት፤ በትምህርትና በፈጠራ የምንኖርበት አዲስ ዘመን ማለት ነዉ፡፡ ስለሆነም እግዚያአብሔር እየሱስ ክርስቶስን እንዲወለድ ያደረገዉ በአምሳሉ ፍፁም እዉነት አድርጎ የፈጠረንን የሰዉ ልጆች በአዲስ ህይወት ለማስቀጠል መሆኑ መቁጠሪያችን ላይ ይታያል፡፡  የዓመተ ምህረት አህፅሮተ ቃል ዓ.ም ነዉ፡፡ ዓ እና ም ደግሞ ከሰዉ ልጅ ቀኝ አይንና ፊት(ዓ) እና ሁለት አይኖችና ግራ አፍንጫ ሥር (ም) ተቀድተዉ የተወሰዱ መሆናቸዉን በምልከታ ማወቅ ችለናል፡፡ ስለዚህ ፍፁም ሁለንታዊ እዉነቶችን የፈጠረዉ ከፍፁም በላዩ እግዚያአብሄር  መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነዉ፡፡

በመሆኑም እየሱስ ክርስቶስ የተወለደዉ መቼ ነበር የሚለዉን ጥያቄ በቀላሉ መመለስ የቻልነዉ ከአዉደ ጳጉሜ 6 ሳምንት መስመራዊ እኩልታዎች ዉስጥ ቀጥሎ የሰኞእለት መስመራዊ እኩልታ ወስደን በመጠቀም ነዉ፡፡

ከእኩልታዉ በስተግራ የተመለከተዉ ጥገኛ ተለዋዋጭ ፊደል ሰኞ ጳጉሜ 6 ለስንተኛ ጊዜ ሰኞእለት ላይ ዉሎ እንደነበር የምናዉቅበት ቁጥር ሲሆን፤ ከኡኩልታዉ በስተቀኝ የተመለከተዉ ኢ-ጥገኛ ተለዋዋጭ ፊደል ዓ4 ማለት አዉደ ጳጉሜ 6 ሰኞእለት ላይ የዋለበት ምድብ ሦሥት ዓመት ምን እንደነበር ወይም እንደሚሆን የሚያሳይ ቁጥር ነዉ፡፡የመስመራዊ ግድለት 1/28 እና ተደማሪ ክፍልፋይ 1/28 የማይለዋወጡ አሃዶች ናቸዉ፡፡ በመሆኑም በጥገኛ ተለዋዋጭ ሰኞ ቦታ ቁጥር 215ን ተክተን ሂሳቡን ስናሰላ ፤ የኢ-ጥገኛ ተለዋዋጭ ምድብ ሦሥት ዓመተ ፍዳ (ዓ4 ) ዋጋ 6019  ሁኖ ተገኝቷል፡፡

ይህም እየሱስ ክርስቶስ የተወለደዉ ሰኞእለት፤ ጳጉሜ 6፤6019 አ.ፍ እንደተፈፀመ፤ ፀሃይ ፍንጥቅ ባለችበት ቅጽበት ላይ በቀጠለዉ ማክሰኞእለት፤ መስከረም 1፤ 0 ዓ.ም ምድብ አንድ ዓመት ላይ ነበር ማለት ነዉ፡፡ በመሆኑም ቁጥር 0 (ዜሮ) በአማርኛ ዞሮ ገጠመ የሚል ፍች ይዞ ስለሚገኝ፤ በእርግጥም የምድብ አንድ ዓመት መነሻ ቁጥር የተፈጥሮ ቁጥር 0 ትክክል ነዉ፡፡  እንዲሁም የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ  በሦሥት ምድብ አራት ዓመት ህግ የተሰራ ስለሆነ ረቡእለት፤ መስከረም 1፤1 ዓ.ም፤ ሃሙስእለት፤ መስከረም 1፤2 ዓ.ም እና አርብእለት፤ መስከረም 1፤3 ዓ.ም ላይ መጀመሩ በትክክል የታወቀ ነዉ፡፡ በመሆኑም የአመተ ምህረት  አራት የመጀመሪያ ዓመቶች 0 የምድብ አንድ፤ 1 እና 2 የምድብ ሁለት እና 3 የምድብ ሦሥት ሲሆኑ፤  የመጀመሪያ የተፈጥሮ ቁጥሮች ሁነዉ ተገኝተዋል፡፡

 1. የተሳሳተዉ ጊዜ አቆጣጠር ቀደም ሲል የጁሊያን እና አሁን የግሪጎሪያኑ ሥለመሆኑ

ከእኛዉ የእየሱስ ክርስቶስ መገለጫ መቁጠሪያችን አንፃር የጁሊያንን አቆጣጠር የጀመረዉ ቱስዴይ፤ ሰብቴምበር 12፤ 7 አ.ዶ ምድብ ሦስት ዓመት፤ ዊድንስዴይ፤ ሰብቴምበር 11፤ 8 አ.ዶ ምድብ አንድ ዓመት  ተርስዴይ፤ሰብቴምበር 11፤ 9 አ.ዶ ምድብ ሁለት አንደኛ እና ፍራይዴይ፤ ሰብቴምበር 11፤ 10 አ.ዶ ምድብ ሁለት ሁለተኛ ላይ ሁኖ ተገኝቷል፡፡ ስለዚህ የአኖ ዶሚኒ አራት የመጀመሪያ አመቶች 7  የምድብ ሦስት፤ 8 የምድብ አንድ፤ 9ና 10 የምድብ ሁለት አንደኛና ሁለተኛ ነበሩ ማለት ነዉ፡፡ በመሆኑም አኖ ዶሚኒ የመጀመሪያዉን ሦስት ምድብ አራት ዓመት 0፤1ና2 እና 3 ብቻ ሳይሆን ከሁለተኛዉ ሦሥት ምድብ አራት ዓመቶች ዉሥጥ  4፤ 5 እና 6ን ዘሏቸዋል፡፡

 

3.1 የጁሊያን አኖ ዶሚኒ ከ 7 ዓመት በላይ የተሳሳተዉ ለምንድን ነዉ?

ከላይ የተመለከተዉ ትንተና የጁሊያን አኖ ዶሚኒ ከኢትዮጵያዉ ዓመተ ምህረት ከ7ዓመት በላይ አሳስቶ  መጀመሩን ያሳያል፡፡ ነገር ግን ለምን ዘሎ እንደጀመረ አያሳይም፡፡ ለምን ከ7 ዓመት በላይ  ዘሎ ሊጀምር ቻለ ለሚለዉ ጥያቄ መልስ መገኘት አለበት፡፡ በቅድሚያ ወደ መልሱ የሚወሰዱን ሁለት ሳይንሳዊ የጊዜ ዥረቶች እና አንድ ኢሳይንሳዊ  ዥረት አለ፡፡ የመጀመሪያዉ ሳይንሳዊ የጊዜ ዥረት መነሻ ጥንት የባቢሊዮን ሰዎች ሲሆኑ፤ የጊዜ ዥረት ሳይንስን ወደ አማካይ ፀሃይ ዓመት የለወጡት ጥንት የግሪክ ሰዎች ናቸዉ፡፡ ጥንት የባቢሊዮን ሰዎች  ምድር ፀሃይን ለመዞር የሚወስድባት ጊዜ 360 እለት ነዉ ብለዉ ያምኑ ስለነበር (1ኛ) አሁን የምንጠቀምበትን የክብ ዙሪያ መለኪያ 360 ዘዌ ሰርተዉ የሰጡን  እነርሱ ናቸዉ፡፡ (2ኛ) አመት ማለት 360 እለት የያዘ ጊዜ ስለነበር በ12 ወሮች እያንዳነዱን ወር በ30 እለት መድበዉ ይጠቀሙም ነበር፡፡ (3ኛ) እለት ማለት ከ360 እለታት ዉስጥ አንዱ ወይም እያንዳንዱ ነበር ማለት ነዉ፡፡ (4ኛ) እለት 24 ሰዓት፤ ሰዓት 60 ደቂቃ እና ደቂቃ 60 ሰከንድ አድረገዉ መጠቀማቸዉ ይነገራል፡፡ የባይብል ዓመት ማለት 12 ወር በ30 እለት መደብ የያዘ መሆኑን A Bibilical“time”=12x30 days=360.(Rev.11:2,3;12:6,14) ተዛማች ጽሁፎች ያሳያሉ፡፡

ቀጥለዉ ጥንት የግሪክ ሰዎች (1ኛ) በባቢሊዮን 360 እለት ላይ  5.25 እለት ጨምረዉ ወደ አማካይ ፀሃይ ዓመት 365.25 እለት የለወጡት  5500 ዓመተ ፍዳ ላይ ነበር፡፡ ተጨማሪዉ 5.25 እለት በኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ላይ ከነሐሴ ወር ቀጥሎ 5 እና 6 እለት ይዞ የተካተተዉ ጳጉሜ እጅግ ዘመናዊ ነዉ፡፡(2ኛ) ከፀሃይ የሚቀዳዉን የባቢሊዮን 360 ዘዌ ተጠቅሞ የሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃት ምድረ ሰማይ ፀሃይ መመላለሻ መስመሮች ሰኔ 14 (ትሮፒካል ካንሰር፡- ከ23.5°ምሥረቅ ሰሜን ሞቃት ወደ 156.5° ምዕራብ ሰሜን ሞቃት የተዘረጋ መስመር) እና ታህሳስ 12 (ትሮፒካል ካፕሪኮረን፡-ከ203.5°ምዕራብ ደቡብ ሞቃት ወደ 336.5° ምሥራቅ ደቡብ ሞቃት የተሰመረ) መሆናቸዉን ፓረማኒደስ የፈጠረዉ እዛዉ 5500 አመተ ፍዳ  ዉስጥ ነዉ፡፡

ነገር ግን ኢሳይነሳዊ የጊዜ ዥረት ማለት የጁሊያንን መቁጠሪያ በአማካይ ፀሃይ ዓመት 365.25 እለት እጅግ ዘግይተዉ ያሰሩት 46 ቅድመ ክርስቶስ ላይ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፤ 12ቱን ወሮች፤ 7 ወሮች ባለ 31 እለት 4 ወሮች ባለ 30 እለትና 1 ባለ 28ና 29 እለት የደለደሉት  ተጨማሪዉን 5.25 እለት ካለ ዘዴ በመበተን መሆኑን ያጠቃልላል፡፡ ስለዚህ መጀመሪያዉኑ የጁሊያን አቆጣጠር ከ7 ዓመት በላይ  አሳስተዉ ሊጀምሩ የቻሉት

 • ቅድመ ክርስቶስ ዘመንን ወደ አኖ ዶሚኒ አቆጣጠር ሲለዉጡ እርሱ ከመወለዱ በፊት በ519 ዓመታት አጉድለዋል፡፡
 • እርሱ ከመወለዱ ነፊት በ519 ዓመት አጉድለዋል ማለት ለ519 ጊዜ ያላካተቱት 5.25 እለት እንደነበር ተገኝቷል፡፡
 • ለ519 ጊዜ ያላካተቱት 5.25 እለት ተጠራቅሞ ወደ አማካይ የፀሃይ ዓመት ሲለወጥ 7.46 ዓመት ወይም 7 ዓመት፤ ከ5ወር፤ 2 ሳምንት፤1 እለት፤ 19 ሰዓት እና 30 ደቂቃ የሚያህል ጊዜ እንደነበረ ታዉቋል፡፡
 • ከ0 እስከ 6 ድረስ መኖር የነበረባቸዉን አኖ ዶሚኒዎች እንዳይኖሩ አድርጓል፡፡
 • ከኢትዮጵያ አቆጣጠር አንፃር አቆጣጠራቸዉን በሦሥት ምድብ አራት ዓመት መነሻ ምድብ አንድ ዓመት ላይ ሳይሆን በምድብ ሦስት ዓመት ቱስዴይ፤ ሰብቴምበር 12፤ 7 አ.ዶ መጀመራቸዉ ታዉቋል፡፡

ስለዚህ ከላይ የተመለከቱትን ጭብጦች ተከራካሪዉ ቢያወቁ ኖሮ አሁን ኢትዮጵያ የምትጠቀመዉ የዘመን አቆጣጠር  ከጁሊያን ቀን መቁጠሪያ ጋር አንድ  ነዉ ማለታቸዉ ከማሳፈር በላይ መሆኑን ያዉቁት ነበር፡፡

3.2 የግሪጎሪያን መቁጠሪያ አራት ተጨማሪ ቅሌቶች

የጁሊያንን ቀን መቁጠሪያ የተጠቀሙት እስከ ፍራይዴይ፤ ኦክቶበር 4፤ 1582 አ.ዶ ድረስ ነዉ፡፡ ከሳተርዴይ፤ ኦክቶበር 5፤1582 አ.ዶ ጀምሮ ግን የግሪጎሪያን ቀን መቁጠሪያ በሚል ስሙን ለዉጠዉት ይገኛል፡፡ ስለዚህ የጁሊያን ቀን መቁጠሪያ እና የግሪጎሪያን መቁጠሪያ ተከታታይና አንድ አይነት ናቸዉ፡፡ ሆኖም ግን የምሥራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ጠባብ ቀዝቃዛ ምድር ቀርፋፋ ሹረትና ዙረት መሆኑን ባለመገንዘባቸዉ የተነሳ በግሪጎሪያን መቁጠሪያ የተሰሩ አራት ተጨማሪ ቅሌቶች ይገኛሉ፡፡

 • አማካይ የፀሃይ ዓመት 365 እለት፤ 5 ሰዓት፤ 48 ደቂቃ ከ46 ሰከንድ ነዉ ሲሉ ያላገባብ 11 ደቂቃ ከ14 ሰከንድ ቀንሰዉ ገምተዋ፡፡
 • ባሳሳቱት ግምት ላይ ተመስርተዉ በጁሊያን መቁጠሪያ ኦክቶበር 4 ማግስት ኦክቶበር 5 ከመሆን ፈንታ፤ ኦክቶበር 15፤1582 አ.ዶ ብለን የግሪጎሪያንን መቁጠሪያ የቀጠልነዉ 11 እለት በመሰረዝ ጭምር ነዉ ሲሉ ፅፈዉት የሚገኘዉ መረጃ ከኢትዮጵያ መቁጠሪያ አንፃር ሃሰት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ምንም የተሰረዘ ጊዜ የለም፡፡
 • ስለዚህ ፌብሩዋሪ 28ን በየአራት አመት 29 የሚለዉጡት ያጎደሉትን ከ44 ደቂቃ በላይ ከየት እያመጡ ነዉ የሚለዉ ጥያቄ ሲፈተሽ፤ በሞቃት ምድር ፈጣን ቅስቃሴ መሰረት ሰርተዉ በእጃቸዉ ያሰሩትን እና በግርግዳ ላይ የሰቀሉትን ሰዓት ወደ ኋላ እየጠመዘዙ መሆኑ ታዉቋል፡፡
 • በየ400 ዓመት አንዴ ሌላ 1 እለት ይተርፋል ያሉት ትንቢት የተሳሳተ ነዉ ፡፡

በመሆኑም ተሟጓቹ የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ የተፃረሩት መቁጠሪያዉን ስለማያዉቁት ብቻ ሳይሆን ከላይ በግሪጎሪያኑ የተሰሩትን አራት ተጨማሪ ቅሌቶች ትክክል ነዉ ብለዉ በመቀበላቸዉ የተነሳ መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ፡፡

 1. ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ተከራካሪዉ ፍፁም የሆነዉንና ከአጠቃላይ ምድር 84 እጅ በላይ የሚሸፍነዉን የኢትዮጵያን ቀን መቁጠሪያ ከጁሊያን መቁጠሪያ ጋር አንድ አይነት ነዉ፤ መሆኑም አያሳፍር! ሲሉ የበየኑት ብያኔ ከረገጡት ምስራቅ ሰሜን ሰፊ ሞቀት ምድር ሰማይ የተላቀቁ መሆናቸዉን ብቻ ሳይሆን ከ16 እጅ በታች በሆነዉ የሰሜንና ደቡብ ጠባብ ቀዝቃዛና ቀርፋፋ ምድሩ የግሪጎሪያን መቁጠሪያ አስተክተዉት ከሚገኙት ሰዎች ዉስጥ አንዱ መሆናቸዉን አረጋግጠዋል፡፡ መቁጠሪያችንን  በግሪግጎሪያን መቁጠሪያ አስተክተዉት ከሚገኙት ዉሥጥ ደግሞ ዋነዎቹ የግእዝ ሳምንት ስሞች (ሰኞ፤ ማክሰኞ፤… እሁድ) እና አነኝህን ስሞች በእንግሊዝ ሳምንት በዉርስ (ሰኞን መንዴይ፤ ማክሰኞን ቱስደየይ… እሁድን ሰንዴይ) ተርጉመዉ በመጠቀም ላይ የሚገኙ ሰዎች ናቸዉ፡፡ ነገር ግን የእንግሊዝ ሰዎች በሳይስና ቴክኖሎጂ ተደግፈዉ በጁሊያን ሳምንት ስሞች ላይ ዴይን ጨምረዉ ከመንዴይ እስከ ሰንዴይ አድርገዉ የፈጠሩት 1752 አ.ዶ ላይ ነበር፡፡ ስለዚህ የእንጊለዝ ሳምንት በሰሜንና ደቡብ ጠባብ ቀዝቃዛና ቀርፋፋ ምድር ዉሥጥ የሚከሰት 7 ተከታታይ እለታት ናቸዉ፡፡

ስለዚህ የግእዝን ሳምንት ከዉርስ ትረጉም በማላቀቅ የምሥራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃትና ፈጣን ምድር ዉስጥ የሚከሰቱ 7 ተከታታይ ፈጣን እለቶች ማሳየት የሚችሉት በእያንዳንዳቸዉ ላይ እለት ጨምረን ወደ አማርኛ ሳምንት ለዉጠን መጠቀም ስንችል ብቻ ነዉ፡፡ በመሆኑም የአማርኛ ሳምንት ሰኞእለት(Segnoelt)፤ ማክሰኞእለት (Maksegnoelt)፤ ረቡዕለት(Robelt)፤ ሃሙስእለት(Hamuselt)፤ አርብእለት (Arbelt)፤ ቅዳሜእለት(Kidamelt) እና እሁድእለት (Ehudelt) ሁነዉ ተፈጥረዋ፡፡ የእንግሊዘኛ ሳምንት በሞቃት ምድር ዉሥጥ መከሰት ስለማይችል በአማርኛ ሳምንት ማንኛዉም ክስተትና ስራ እንዲመዘገብባቸዉ በማድረግ ተፈጥሮያዊ፤ ጂኦ-ፖለቲካዊ፤ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊ፤ሳይንሳዊ እና ሃይማኖታዊ ጥቅሞችን ማግኘት የግድ ይኖርብናል፡፡ እንዲሁም የአማርኛ ሳምንት ማለት የእንግሊዘኛ ሳምንት ሞቃት ምድር ዉስጥ የማይከሰቱና የማያገለግሉ መሆናቸዉን በጥንታዊ እና ዘመናዊ ትምህርት ዉስጥ አካትተን በማስተማር ሁለቱንም አለሞች በቀላሉ የምንፈጥርበትና የምንመራበት  ዘዴ ማለት ነዉ፡፡ ለምሳሌ፤ ዛሬ አርብእለት፤ ሃምሌ 28፤ 2009 ዓ.ም የምሥራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃትና ፈጣን ምድር እለት ማለት ሲሆን፤ ፍራይዴይ፤ ኦገስት 4፤ 2017 አ.ዶ ግን የምሥራቅ ምዕራብ ሰሜንና ደቡብ ጠባብ ቀዝቃዛና ቀርፋፋ ምድር እለት ማለት ነዉ፡፡  ሌሎቹንም እለቶች በዚሁ ዘዴ ልንጠቀምባቸዉ የግድ ይላል፡፡ በመጨረሻ በተቃዉሞ ሥም አዉደ ጳጉሜ 6 በጥንታዊ አስተምሮት ዘዴ ፍፁም አለመታወቁን በሚመለከት ሁለተኛ የፅሁፍ ምስክርነት በመስጠትዎ እና የግእዝን ሳምንት  ወደ አማርኛ ሳምንት መለወጥ እንድንችል ላበረከቱት የተቀዉሞ መጣጥፍ በራሴና በአንባቢዎች ስም የተለመደዉን ምስጋና አቀርባለሁ፡፡

ዋቢፅኁፎች

 • ሰለሞን አበበ (2006 ዓ.ም )፡፡ ጳጉሜ 6 ስለየትኛዉ ዘመን መቁጠሪያ ነዉ የሚናገረዉ?ጥቅምት 23፤2006 ዓ.ም አዲስ አድማስ ሳምንታዊ ጋዜጣ፡፡
 • አብነት ስሜ (2007ና 2008 ዓ.ም)፡፡ እመቤቴ ሆይ ጳጉሜ የዘመን ቆጠራችን ጉዳይ መስከረም 1፤2008 ዓ.ም አዲስ አድማስ ሳምንታዊ ጋዜጣ፡፡
 • የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ (2006 ዓ.ም)፤ አማርኛ መዝገበ ቃላት፤ አዲስ አበባ ዩኒቭርሲቲ፡፡
 • ጌታቸዉ ኃይሌ (2006 ዓ.ም)፡፡ ባሕረ ሐሳብ፤ የዘመን ቆጠራ ቅርሳችን ከታሪክ ማሰታወሻ ጋር፡፡ 2ኛ እትም፤ አዲስ አበባ፡፡
 • ፋሲል ጣሰዉ (2007 ዓ.ም)፡፡የጳጉሜ 6 ተቃዉሞ ማፍረሻ ሐምሌ 25፤2007 ዓ.ም፤አዲስ አድማስ ሳምንታዊ ጋዜጣ፤አዲስ አበባ፡፡
 • ------------(2005 ዓ.ም)፡፡ ጳጉሜ 6፤ የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ የማን ነዉ? ባናዊ አሳታሚ ድርጅት፤ አዲስ አበባ፡፡ Microsoft Encart EnyclopidaStandard Edition 2009, software © 1993-2008 Microsoft Corporation).
 • መሰረት ስብሐት ለአብ (1971 ዓ.ም)፤ ትዉፊታዊ ኀሳበ ዘመንና ታሪኩ፤ በኢትዮጵያ ቤት ክርስቲያን አቋም፡፡ ንግድ ማተሚያ ቤት፤ አዲስ አበባ፡፡

Design By: 0913511849